የንስር አሞራ ሚስጥራዊ ተፈጥሮ

 

ፍጥረታት ሁሉ ይችን ምድር ሲወርሱ የተሰጣቸው አስገራሚና ልዩ ውብ ተፈጥሮ አላቸው፡፡ ከነዚህ የተፈጥሮ ፀጋ ከተሰጣቸው ድንቅ የምድራችን ፍጥረታት መካከል አንዱ የንስር አሞራ ነው፡፡ የንስር አሞራ ምድቡ ከአእዋፍ ወገን ሲሆን ተፈጥሮ የሰጠችው ድንቅ ሚስጥራዊ ተፈጥሮ ግን የተለየ ያደርገዋል፡፡

 

 ዛሬ በዓለማችን የሰው ልጆች አማካኝ የዕድሜ ጣሪያ 65 ዓመት በሆነበት ዘመን ንስር አሞራ ከአዕዋፋት ዘር 70 ዓመት የመኖር ፀጋ ተፈጥሮ የቸረችው የእድሜ ባለጸጋ ነዉ። አስገራሚው ነገር ይህ ድንቅ አእዋፍ ዕድሜው 40 ሲሆን ተፈጥሮ ሁለት አማራጮችን በፊቱ ታቀርብለታለች፤ እንደ አማረበት መሞት ወይም እድሜውን  ወደ 70 አመት ከፍ ለማድረግ ተፈጥሮ ያዘጋጀችለትን የመከራና የስቃይ ጽዋ ምሬት አጣፍጦ በመጎንጨት ተጨማሪ 30 ዓመት የድል ዋንጫ መቀዳጀት፡፡

  ንስር አሞራ ከተፈለፈለ ጀምሮ 40 ዓመት ከኖረ በኋላ ምግቡን ለማደን የሚገለገልበት ጥፍሮቹ ከመጠን በላይ ስለሚያድጉ ምግቡን መሬት ላይ ማንሳት ያቅተዋል፡፡ አጥንትን ሳይቀር መስበር አቅም ያለው መንቁሩ ስለሚታጠፍና ስለሚጣመም ምግቡን እንደወትሮው መመገብ ይሳነዋል፡፡ ክንፉና በአካሉ ላይ ያሉ ላባዎች ስለሚከብዱት፤ያ ሰማየ ሰማያትን እየሰነጠቀ እንደ ሚግ ጀት ይበር የነበረው ሀይሉ ይክደዋል፡፡  በዚህ ወቅት ድንቅ የአእዋፍ ዘር ንስር አሞራ በሁለት ዉሳኔዎች አጣብቂኝ ውስጥ ይወድቃል፡፡ የመጀመሪያው አማራጭ ከዚህ ካረጀ አካሉ ጋር ዝም ብሎ በመቀመጥ ሞቱን መጠበቅ፤ ወይም 5 ወር የሚፈጅ ስቃይና መከራ ያለበት መስዋእትነትን ከፍሎ ቀሪውን 30 አመቱን መውለድ፡፡

 

የንስር አሞራ ከቀረበለት ሁለት ምርጫዎች ቀሪ 30 ዓመቱን መቀጠል ከሆነ ምርጫው ተፈጥሮ ያዘጋጀችለትን የመከራ ጽዋ መጎንጨት ግድ ይለዋል፡፡ ይኸውም ከፍተኛ ተራራ ላይ በመዉጣት የብቻውን ጎጆ ቀልሶ ሱባኤ መግባት ይኖርበታል። በሱባኤውም ወቅት የመጀመርያ ስራዉ የአፉን መንቁር ከአለት ጋር በማጋጨት ነቅሎ መጣል ነው፡፡ ይህን ካደረገ በኋላ አዲስ መንቁር ያወጣለታል፡፡ መንቁሩ እስኪያድግ ድረስ ታግሶ በጎጆው ምንም አይነት ምግብ ሳይመገብ በፆም መቆየት ግዴታው ይሆናል፡፡

 

 

የትዕግስቱ ፍሬ በሆነው በአዲሱ መንቁሩ የገዛ እግሩን አሮጌ ጥፍር ነቃቅሎ ይጥለዋል። አዲሱ የእግር ጥፍር ከበቀለለት በኋላ ደግሞ ይህንን አዲስ ጥፍር እንደመሳርያ በመጠቀም በሰዉነቱ የተጣበቁትን እንዳይበር እንቅፋት የሆኑትን የገዘፉና ያረጁ ላባዎችን ነቃቅሎ ይጥላል። በምትኩ አዲስ ላባ ያበቅላል። የሱባኤውን 5ወር በዚህ መልኩ በጀግንነት ከተወጣ በኋላ እንደገና ራሱን በራሱ ወልዶና ወጣት ሆኖ ወደ ንስሮች መንደር ብቅ ይላል፡፡ በእድሜው ላይ 30 አመት ጨምሮ በበረራው ሰማየ ሰማያትን እየሰነጠቀ ከፍ ብሎ እየበረረ ህይወትንና ደስታን በውሳኔው ባተረፈው 30 አመት ሙሉ በከፍታዎች ሁሉ ላይ በድል፣ በግርማና በሞገስ ይበራል ፡፡አስደናቂው "# የንሥር " ተፈጥሮ

 

አስተያየቶች